ለምን ሕፃናትን እናጠምቃለን?

By Pastor Josh Sullivan (translation:- Augsburg Catholic)

ለምን ሕፃናትን እናጠምቃለን?

ጥያቄ 1 ፦ አንድ ጨቅላ ሕፃን መጠመቅን እምቢ ሊል አይችልም። እና “እመኑ፣ ተጠመቁም” ከተባለ፣ ጨቅላ ሕፃን በራሱ ምርጫ ማመን አይችልም። ታዲያ ጨቅላ ሕፃን መጠመቅ አለበት የሚባለው ለምንድን ነው? ከሆነስ፣ ጨቅላ ሕፃንን ገና ሲወለድ አታጠምቁትም ነበርን? ታዲያ ክርስቲያን ያልሆኑ ወላጆች ልጆችስ ምን ይሆናሉ፣ ወደ ገሃነም ይሄዳሉ? በጥንቷ ቤተ ክርስቲያንስ ጨቅላ ሕፃናት ይጠመቁ ነበርን? ማረጋገጫ (ወይም ያመኑትን በአፍ መመስከር) ወዴት ይገባል? አንድ ልጅ እምነቱ ካልተረጋገጠ (በመመስከር) ይድናልን?

ጥያቄ 2 ፦ የቸርች ኦፍ ስዊድን አባል የሆነ ጓደኛ አለኝ፤ የክፍል ጓደኛችን ደግሞ የጴንጤቆስጤ አባል ነው። አሁን ሉተራን የሆነው ጓደኛዬ በ“ነጻ ፈቃድ” ላይ ተመስርቶ የሕፃናትን ጥምቀት መጠራጠር ጀምሮአል ከጴንጤቆስጤው ጎንም ቆሟል። ጥምቀት እንደሚያድን እንዴት ላስረዳው እችላለሁ፣ ምክንያቱም “ነጻ ፈቃድ” በማለት ይመልስልኛልና?

መ፦ ሕፃናትን የምናጠምቅበት ሁለት ቀላል ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው የጥምቀት መለኮታዊ ተቋም (institution) ነው። ሁሉም (አሕዛብ)እንዲጠመቁ መለኮታዊ ትእዛዝ ተሰጥቷል። ሕፃናትም የሕዝብ ክፍል ናቸው። አብዛኛው ፕሮቴስታንት በተለይ ሕፃናትን ለማጥመቅ የተሰጠ ትእዛዝ አይደለም ብሎ ይመልሳል። ነገር ግን አዋቂዎችን፣ ወጣቶችን ወይም አረጋውያንን እንድናጠምቅ ትእዛዝ አለንን? የለም። ለምን? ኢየሱስ “ሁሉንም (አሕዛብ) አጥምቁ” ብሎ ያዘዘው ትእዛዝ እድሜ ስለማይለይ ነው። “ሁሉም (አሕዛብ)” ልክ አዋቂዎችና አረጋውያን እንደያዘው ሁሉ ሕጻናትንም ይጨምራል። ይህ ቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ ሕፃናትን ስታጠምቅ የቆየችበት መሠረታዊ ምክንያት ነው : - ሁሉንም አሕዛብ የማጥመቅ መለኮታዊ ትእዛዝ። ይህን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲሆን እናያዋለን። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 1፡16 “የእስጢፋኖስን ቤተሰብ” እንዳጠመቀ ይናገራል። በሐዋርያት ሥራ 16፡15 ልድያና “ቤተሰብዋ” ተጠምቀዋል። ሐዋርያት ሥራ 16፡33 የፊልጵስዩስ እስር ቤት ጠባቂ “እርሱና ቤተሰቡ ሁሉ” እንደተጠመቁ ይናገራል። ሕፃናት በግልጽ በቤተሰብ ውስጥ ይካተታሉ።

ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው የሕፃናት ጥምቀት ልማድ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያንም ቀጠለ። በ160 ዓ.ም. ገደማ የጻፈው የሊዮኑ ሄሬኔዎስ ሕፃናት እንደሚቀደሱና እንደገና እንደሚወለዱ ይመሰክራል (Against Heresies 2፡22፡4)። በ200ዎቹ መጀመሪያ የጻፈው ሂፖላይተስ የሕፃናት ጥምቀትን ይመሰክራል (The Apostolic Tradition 21፡4)። የእስክንድርያው ኦሪገን ቤተ ክርስቲያን ይህን ልማድ ከሐዋርያት እንደተቀበለች ይጽፋል (Homilies on Leviticus 8፡3፤ Commentaries on Romans 5፡9)። ሌሎች አባቶችም እንደ ካርቴጁ ቅዱስ ቆጵርያኖስ (Letters 64፡2፤ 64፡5)፣ ጎርጎሪዮስ ዘንዚናንዙ (Oration on Holy Baptism 40፡7፤ 40፡28) የሕፃናትን ጥምቀት በጽሀፎቻቸው ውስጥ ይመሰክራሉ። ይህ የሚያስደንቅ አይደለም፤ ምክንያቱም ሐዋርያት ራሳቸው በአዲስ ኪዳን ውስጥ ቀድሞውኑ መላውን ቤተሰብ አጥምቀዋልና።

ሁለተኛው ሕፃናትን የምናጠምቅበት ምክንያት፣ በጥምቀት እግዚአብሔር የሚሰጠው ነገር ስለሚያስፈልጋቸው ነው። ሕፃናትን ማጥመቅ የሚክዱ ሰዎች ይህን የሚያደርጉት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አዳማዊ ኃጢአት (Original Sin) የሚያስተምረውን ስለሚክዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተፈጥሮ መንገድ ማለትም በወንድና በሴት ግንኙነት የተወለዱ ሁሉ ኃጢአተኞች ሆነው እንደሚወለዱ ያስተምራል። ጥምቀት ደሞ እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን እንደገና የእግዚአብሔር ልጆች አድርጎ የሚወልድበት መንገድ ነው። እዚህ ላይ ስለ ነጻ ፈቃድ ስለሚነሳው ልክ ያልሆነ ክርክር መናገር እንችላለን፣ ይኸውም ጥምቀት ኃጢአተኛው እስኪመርጥ ድረስ መዘግየት አለበት የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥምቀት እግዚአብሔር እንደገና የሚወልደን መንገድ እንደሆነ በግልጽ ያስተምራል። ቅዱስ ጳውሎስ ይህንኑ በቲቶ 3፡4-5 በግልጽ ይናገራል፦ “ነገር ግን የመድኃኒታችን የእግዚአብሔር ቸርነትና ሰውን መውደዱ በተገለጠ ጊዜ፥ እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም፤ ” እግዚአብሔር እንዴት ያድነናል? “በዳግም ልደት መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ።” ዳግም መወለድ ማለት እንደገና መፈጠር ወይም እንደገና መወለድ ማለት ነው።

ጳውሎስ ይህን ትምህርት ከየት አገኘው? ከክርስቶስ! እርሱ በዮሐንስ 3፡5 እንዲህ ይላል፦ “እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም። ” ጥምቀት እግዚአብሔር ኃጢአተኞችን የእግዚአብሔር ልጆች አድርጎ የሚወልድበት መንገድ ነው። ይህ ከነጻ ፈቃድ ክርክር ውስጥ ያለውን አየር ያስወጣል። አካላዊ ልደትህ(ከእናትህ ማህፀን)መቼ እንደሚሆን አንተ ወስነህ ነበርን? በፍጹም። ለመንፈሳዊ ልደትህም ተመሳሳይ ነው። ጥምቀት ከእምነት በኋላ ያለው የሰው የመጀመሪያ የታዛዥነት ሥራ ወይም የሰው ውሳኔ ነው ብለው የሚናገሩ ሰዎች፣ ክርስቶስና ጳውሎስ ሁለቱም ስለ ጥምቀት የተናገሩትን አልተረዱም። ጥምቀት መንፈሳዊ ዳግም ልደት ነው፤ በሥጋ መቼ እንደምትወለድ ልትወስን እንዳልቻልክ ሁሉ፣ በውኃና በቃል እንደገና ለመወለድም ልትወስን አትችልም። ለመጠመቅ የሚስማማ አዋቂ እንኳ ይህን የሚያደርገው ጌታ ቀድሞ በዚያ አዋቂ ልብ ውስጥ በቃል ስብከት አማካኝነት እምነትን ስለፈጠረለት ነው። ከነጻ ፈቃድ የሚነሳው ክርክር ውኃ አያነሳም፤ ምክንያቱም መንፈሳዊ በሆነ ነገር ላይ ስናወራ ማንም ነጻ ፈቃድ የለውም፤ ይልቁንም በተፈጥሮ ዕውር፣ የሞተ፣ የእግዚአብሔር ጠላት ነውና።

ቅዱስ ጴጥሮስም በ1 ጴጥሮስ 3፡21 ተመሳሳይ ነገር ይናገራል፦ “ ይህም ውኃ ደግሞ ማለት ጥምቅት ምሳሌው ሆኖ አሁን ያድነናል፥ የሰውነትን እድፍ ማስወገድ አይደለም፥ ለእግዚአብሔር የበጎ ሕሊና ልመና ነው እንጂ፥ ይህም በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ ነው፤ ” ጥምቀት በጎ ሕሊና የሚሰጠው እንዴት ነው? ምክንያቱም በእርሱ ውስጥ እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ስለሚለን ነው። ያው ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት በሐዋርያት ሥራ 2፡38-39 ተመሳሳይ ነገር ይናገራል። “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።

የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና::” ጥምቀት ለሕፃናት ሲከለከል፣ መጽሐፍ ቅዱስም እየተካደ ነው፤ ይኸውም መጀመሪያ ሰዎች ሁሉ ኃጢአተኞች ሆነው እንደሚወለዱ፣ ሁለተኛም ጥምቀት ለሰዎች ሁሉ ያለ እድሜ ልዩነት እንደሚሰጥ የሚያስተምረውን ትምህርት ነው። በአዋቂው ውስጥ እምነት በቅዱስ ሚስጥሩ በኩል ይረጋገጣል፣ ይጠናከራልም። በጨቅላ ሕፃኑ ውስጥ ግን እምነት የሚፈጠረው ከምድራዊው ንጥረ ነገር ጋር(ውኃ)በተያያዘው ቃል አማካኝነት ነው።

አንዳንዶች ሕፃናት ማመን አይችሉም ብለው ይመልሱ ይሆናል። ነገር ግን ይህም መጽሐፍ ቅዱስን ያለማወቅ ያሳያል። በመዝሙር 22፡9 ዳዊት በእናቱ ጡት ላይ እያለ በእግዚአብሔር ላይ ስለ መታመኑ ይዘምራል። በማቴዎስ 18፡6 ኢየሱስ “በእኔ የሚያምኑትን ታናናሾች” በማለት ያስጠነቅቃል። ምናልባት ለታናናሽ ልጆች ስላለው የክርስቶስ ፈቃድ በተሻለ የምናየው ቦታ ማርቆስ 10 ነው። ታናናሽ ልጆች ለቡራኬው ወደ ኢየሱስ ይመጡ ነበር። ኢየሱስ ምን አለ? “ ልጆች ወደ እኔ ይምጡ፤ አትከልክሏቸውም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደነዚህ ላሉት ናትና።” ታናናሽ ልጆች ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባቸው ናቸው፣ ይህም ለሁሉም ልጆች ማለት ሳይሆን፣ ወደ እርሱ ለመጡና በእርሱ ለተባረኩ እንደነዚህ ላሉት ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት ወደ ኢየሱስ ለመጡት ታናናሽ ልጆች ከተነገረ፣ ሕፃናትና ታናናሽ ልጆች መጠመቅ አለባቸው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ በዮሐንስ 3፡5 እንደተናገረው፣ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባው በዚያ መንገድ ነውና። ልጆች ዛሬ ወደ ኢየሱስ የሚመጡት፣ ኃጢአትን ይቅር ለማለት፣ ድኅነትን ለመስጠትና የዘላለም ሕይወትን ለመስጠት እንደሚገኝ ቃል ወደገባባቸው ስፍራዎች በማምጣት ነው።

ይህ ማለት ክርስቲያን ላልሆኑ ወላጆች ልጆች፣ ልክ እንደ ወላጆቻቸው፣ ገና በኃጢአታቸው ውስጥ ናቸው፤ የእግዚአብሔር ቁጣም ወላጆቻቸው ንስሓ እስኪገቡና እነርሱን እንዲጠመቁ እስከሚያመጧቸው ድረስ፣ ወይም እነርሱ ራሳቸው አዋቂ እስኪሆኑና መንፈስ ቅዱስ በቃል አማካኝነት በእነርሱ ላይ እስኪሠራ ድረስ በእነርሱ ላይ ይኖራል። የእግዚአብሔር መንግሥት የልጆች ሁሉ ሳይሆን፣ ለእርሱ ለቀረቡት ብቻ ነው።

ስለ confirmation(ያመንነውን በአፍ መናገር ወይም መመስከር)፣ ማረጋገጫ ማለት ወጣት አዋቂዎች የተጠመቁበትን እምነት በአደባባይ የሚመሰክሩበት ጊዜ ነው። ይህ ወጣቱ አዋቂ የክርስትና እምነትን ተረድቶ በሰዎች ፊት እንዲመሰክር ከትምህርት ጊዜ (ከእምነት ማጽኛ ትምህርት)በኋላ መከናወን ያለበት ነው ። ማረጋገጫ(confirmation) መለኮታዊ ተቋም ስለሌለው፣ በሰው የተደነገገ ሥርዓት ስለሆነ፣ ለድኅነት አስፈላጊ አይደለም። ነገር ግን የተጠመቁትን በእምነት ለማስተማር ጠቃሚ ነው፣ ስለዚህም የክርስትና እምነትን በአደባባይ ሊመሰክሩ ይችላሉ።

ለምን ሕፃናትን እናጠምቃለን? ክርስቶስ ሁሉንም ሰው እንድናጠምቅ ያዘናል፤ በጥምቀት አማካኝነትም ክርስቶስ በጣም ትንንሾቹንም ጨምሮ ለምስኪን ኃጢአተኞች የማዳን በረከቶቹን ይሰጣል።

ቄስ ጆሽ ሱሊቨን (Holy cross Lutheran church )

ትርጉም :- Augsburg Catholic